ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ በመተሃራ ዘመናዊ የኤክስፖርት ቄራ አስመረቀ

በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር በዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚመራው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አባል የሆነው ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግል ማኅበር በመተሃራ ዘመናዊ የኤክስፖርት ቄራ የማሻሻያ ግንባታ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በተሳካ ሁኔታ ገንብቶ ሚያዝያ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. አስመረቀ፡፡
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር፣ የመተሃራ ከተማ መስተዳድር ጽ/ቤት፣ የፈንታሌ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት እና የአካባቢው ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም የሀገርና የውጭ ገበያ ድርጅቶችና ባለሙያዎች፣ የኤልፎራ የገበያ ማዕከል ደንበኞች እና የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በዚህ የኤክስፖርት ቄራ የማሻሻያ ግንባታ ሥራ ምርቃት ላይ አቶ ዘለቀ መንግሥቴ የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ስለፕሮጀክቱ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኩባንያው ትኩስ የእንስሳት ሥጋን ከነአጥንቱ (ካርካስ) በጥራት ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ እንዲያስችለው ያስገነባው የእርድ ማከናወኛ ቦታ በዘመናዊ የማረጃ ማሽን የተደራጀ እና በአንድ ጊዜ 18 ቶን የበግና የፍየል እርድ በማከናወን በማቀዝቀዣ ቦታ በማቆየት ለሽያጭ ማቅረብ የሚችል ነው፡፡ በዛሬው ዕለት የተመረቀው የመተሃራ ቄራ ኩባንያው ካሉት ስድስት ቄራዎች አንዱ ነው፡፡ የመተሃራ ቄራ በሣምንት ሦስት ቀን በሚያከናውነው እርድ 54 ቶን፤ በወር 216 ቶን፤ በ11 ወራት ደግሞ 2,400 ቶን ሥጋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችለው ዘመናዊ ቄራ ሲሆን፤ ለሥጋው ጥራት የሚያስፈልገው የሙቀት መቆጣጠሪያ መሣሪያም በሚገባ የተገጠመለት ነው፡፡ ይህም አሁን ባለው የኤክስፖርት ዋጋ ሲሰላ በዓመት 12 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያህል ገቢ እንደሚያገኝ ይገመታል፡፡
ቄራው የዓመቱን የሥጋ አቅርቦት ለማሟላት የሚያስፈልገው የቁም እንስሳት ብዛት (በግና ፍየል) 360,000 ያህል በመሆኑ ለአካባቢው አርብቶ አደር ህብረተሰብ ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡
ቄራው በቁም እንስሳት ማቆያ በረቶቹ 10,000 አነስተኛ እንስሳትና 4,000 የዳልጋ ከብቶች የመያዝ አቅም አለው፡፡ በዕርድ ወቅት የተረፈ ምርት ማስወገጃ እንዲሁም ምርቱን ወደ ውጭ ለመላክ ወደ አየር መንገድ መውሰጃ ማቀዝቀዣ በተገጠመላቸው ዘመናዊ መኪናዎች የተደራጀ ነው፡፡ ቄራው የምርት ሂደቱን የሚያግዙ ቢሮዎች፣ የቤተ-ሙከራ፣ የልብስ መቀየሪያና መፀዳጃ እንዲሁም የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች አሉት፡፡ በቀጣይ ቄራው በሙሉ አቅሙ ሥራ መሥራት ሲችል ለ200 ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡
የመተሃራ ቄራ እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም ከግል ባለሀብት የተገዛ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ ከግንቦት ወር 2008 ዓ.ም በግብርና ሚኒስቴር እና ከተባበሩት አረም ኤምሬት የመጡ የመስኩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እንዲሁም የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እፅዋት ጤና እና ቁጥጥር ጥራት ባለሙያዎች በተከታታይ የሰጡትን ሙያዊ የማሻሻያ ሀሳቦችን በመቀበል ሥራው በ2010 ተጀምሯል፡፡ የቄራ ማሻሻሉ ሥራ በኤልፎራ ባለሙያዎች እና በአብደላ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ኢስታብልሽንመንት የተባለ የውጭ ድርጅት ጥምረት የተከናወነ ሲሆን፤ሳማራ ትሬዲንግ ኢስታብልሽመንት የተባለ የውጪ ድርጅትም በተባባሪነት ተሳትፏል፡፡
ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግል ማህበር በዋናነት በግብርና ልማት በሥጋ ምርት ኢንዱስትሪ፣ በዶሮ ልማትና መሰል አገልግሎት በመሰማራት ምርትና አገልግሎቱን ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ በዘርፉ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡