በሚድሮክ ኢትዮጵያ እህትማማችና ተዛማጅ ኩባንያ ሠራተኞች ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የቦንድ ግዢ አካሄዱ
| የሚድሮክ ኢትዮጵያ እህትማማች እና ተዛማጅ ኩባንያዎች ሠራተኞች ለህዳሴው ግድብ ማሠሪያ ከ26ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በማውጣት የቦንድ ግዢ አከናወኑ፡፡
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዳራሽ ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም. የቦንድ ግዢው በተፈፀመበት ወቅት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሠርና የዕርዳታ አሠባሳቢው ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የቦንዱ ግዢ ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ለምታከናውነው ልማት ዋና አንቀሳቃሽ ለሆነው የኃይል ማመንጫ ግንባታ የሚውል በመሆኑ የዜግነት ግዴታችንን የመወጣታችን አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር አረጋ ቀደም ሲል ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በድርጅቶቻቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውን ጠቅሰው የየኩባንያዎቹ ሠራተኞች የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ስላለባቸው የቦንዱ ግዢ መፈፀሙን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ የ26 ሚሊዮን 158 ሺ 350 ብር ቼክ ከዶ/ር አረጋ እጅ በተቀበሉበት ወቅት እንደተናገሩት የሚድሮክ ኢትዮጵያ እህትማማች ኩባንያዎች በግንባር ቀደምትነት ግዙፍ የሆነውን የቦንድ ግዢ ማከናወናቸውና ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ ማድረጋቸው ለልማቱ ሥራ የዜግነት ድርሻቸውን በዋናነት እየተወጡ ለመሆናቸው ምስክር ነው ብለዋል፡፡ |
![]() |
| የዕርዳታ አሰባሳቢው ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተክሉ ኃይሌ በበኩላቸው የየኩባንያዎቹ ሠራተኞች በራሳቸው ተነሳሽነት የቦንዱን ግዢ ማከናወናቸው ሀገሪቱ ለተያያዘችው የልማት ተግባር ፈጣን ምላሽ የሰጠ በመሆኑ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በአጭር ጊዜ ማሠባሰብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ | |
