የኮምቦልቻ ብረታ ብረት ምርቶች ኢንዱስትሪ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የማዕረግ ተሸላሚ ሆነ
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በሀገራችን ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀው የ2003 ዓ.ም. መርሀ ግብር በአምራች ድርጅቶች ዘርፍ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አባል የሆነው የኮምቦልቻ ብረታ ብረት ምርቶች ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግል ማኅበር በማዕረግ ተሸለመ፡፡የዘመናዊ ሕንፃ ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግል ማኅበርም የአድናቆት የምሥክር ወረቀት አግኝቷል፡፡
መጋቢት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተካሄደው ልዩ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሽልማቱንና የምሥክር ወረቀቱን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ከአቶ ካሣ ተክለብርሃን እጅ የተቀበሉት የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ጌቱ ሲሆኑ፤ ኩባንያው ለግምገማ በቀረበው ሰባት መሠረታዊ የጥራት መለኪያ መስፈርቶች ተገምግሞ ባሳየው የላቀ ተግባር መሸለሙ ተገልጿል።
በሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሀገሪቱ አምራችና አገልግሎት ሠጪ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ገበያው የሚፈልገውን ምርትና አገልግሎት በጥራት ማዘጋጀት ከቻሉ በዓለም ላይ ያለንን ቦታ በማስፋፋት የሀገራችንን ዕድገት እውን ማድረግ እንችላለን ብለዋል፡፡
አቶ ኃይለማሪያም አያይዘውም ‹‹ለለውጥ ቁርጠኛ ፍላጐት በማሳየት በውድድር ሂደቱ ለተሳተፋችሁ ሁሉ አድናቆቴን እየገለጽኩ ተሸላሚዎችም እንኳን ደስ አላችሁ›› በማለት ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ በበኩላቸው በውድደሩ በሥራ አፈፃፀማቸውና ውጤታማነታቸው ጥራትን ወጥነት ባለው መልኩ አጉልተው በማሳየት ብልጫ በማግኘታቸው ድርጅቶቹ አሸናፊ መሆናቸውን ገልፀው፤ ለሽልማት ያበቃቸውም አሠራራቸው ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያሟላ መሆኑ ስለታመነበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኮምቦልቻ ብረታ ብረት ምርቶች ኢንዱስትሪ፣ መቀሌ ዩኒቨርስቲና ቤቴል ቲቺንግ ሆስፒታል የሁለተኛ ደረጃ የማዕረግ ተሸላሚ ሲሆኑ፤ ዳሸን ቢራ፣ ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ፣ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ አክሲዮን ማኅበር፣ ቢሾፍቱ ሆስፒታል፣ ሐረር ቢራና ብሩህ ተስፋ የመስኖ ውሃ ቴክኖሎጂ የአንደኛ ደረጃ የማዕረግ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በውድድሩ ለመሳተፍ 150 ድርጅቶች ፍላጐት ያሳዩ ቢሆንም፤ የተሳተፉት ግን 52 ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል። በሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።