ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ ከፍተኛ ክምችት ያለው ወርቅ በመተከል ዞን አገኘ
|
ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል |
|
|
ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ልዩ ስሙ ጅላይ በተባለ ቦታ 33,000 ኪሎግራም የወርቅ ክምችት ማግኘቱን የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅና የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር አረጋገጡ፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ሰኔ 30 ቀን 2003 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙት ከአዶላ ከለገደንቢ እና ከኡላኡሎ መልካ ወርቅ ፍለጋ ሥራ በተጨማሪ በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በመተከል ዞን 33,000 ኪሎ ግራም ወይም 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን አውንስ የወርቅ ክምችት ለማግኘት ተችሏል፡፡ የወርቁ ክምችት መጠን የታወቀው ኩባንያው እ.አ.አ. ከ2004 ጀምሮ ለፍለጋ በተሰማራበት የ2,292 ካሬ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ በተለይ ጅላይ በተባለ ቦታ ብቻ የኩባንያው ሠራተኞች በሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎቹ አማካይነት በተደረገ የፍለጋና የቤተሙከራ ቅድመ ጥናት መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡ በመተከል ዞን ለተገነኘው የወርቅ ክምችትና ተጨማሪ የፍለጋ ሥራ የመረጃ ማሰባሰቢያ ቤተሙከራ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በቡለን ከተማ የተቋቋመ ሲሆን፣በዕቅዱ ለተካተቱት ለሰው ኃይል ልማት፣ ለመሣሪያ ማሟያ፣ ለመለዋወጫና ለአላቂ ዕቃዎች ግዢ የሚያገለግል 46 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ዶ/ር አረጋ አስረድተዋል፡፡ |
![]() |
|
የመተከል ወርቅ ግኝት በመስኩ በተሰማሩ የኩባንያው ባለሙያዎች ቅድመጥናት በውጭ ባለሙያዎች ጥናት በመታገዝ አዋጭነቱ ተረጋግጦ በምርት ተግባር ላይ ሲውል እ.አ.አ እስከ 2025 ድረስ የወርቅ ማምረቱ ተግባር የሚቀጥል መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልፀው፤ ሊገኝ ከታሰበው የ786,166 አውንስ የተጣራ ወርቅ 1.18 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም ገቢ 19 ቢሊዮን ብር ይገኛል ተብሎ እንደሚታሰብ አመልክተዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ለወደፊቱ ለሚከናወነው የወርቅ ማምረት ሥራ የባለሙያ እጥረት እንዳያጋጥም እንዲሁም በቀጣይ በማዕድን ዘርፍ ለሚከናወኑት ሥራዎች አጋዥ እንዲሆኑ በማዕድን መሀንዲስነት የትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አካል የሆነው ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ትምህርት ከመስከረም ወር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመስጠት ጥናትና ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ |
|
