ቪዥን አሉሚነም ከዳሸን ባንክ ጋር ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ስምምነት ተፈራረመ
መጋቢት 30 ቀን 2008 ዓ.ም.
* ስምምነቱ የባንኩን ሕንፃ የማስፋፋት ስራ በአሉሚነም እና በግራናይት ለማስዋብ የሚያስችል ነው
![]() |
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አባል የሆነው ቪዥን አሉሚነም ኃ/የተ/የግል ማህበር ዳሸን ባንክ አክስዮን ማህበር ለሚያሰራው የማስፋፊያ ህንፃ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአሉሚነምና የግራናይት ሥራ ለመሥራት ከባንኩ ጋር የ53,283,213.58 ብር ስምምነት መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ተፈራርሟል፡፡
በዕለቱ ስምምነቱን የፈረሙት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው እና የዳሸን ባንክ አክስዮን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው አለሙ መሆናችው ታውቋል፡፡
በዚሁ የፊርማ ሥነ-ስርዓት ላይ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው እንደተናገሩት ዳሸን ባንክ አክስዮን ማህበር፤ ቪዥን አሉሚነምን ለፕሮጀክቱ ሥራ በመምረጡ ትልቅ ኃላፊነት ጥሎብናል፤ ይህንኑም ኃላፊነት በብቃት እንወጣዋለን ብለዋል፡፡ በቀጣይም ከባንኩ ጋር መሰል ሥራዎችን የማካሄዱ ሁኔታ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የዳሽን ባንክ አክስዮን ማህበር ፕሮዚዳንት አቶ አስፋው አለሙ በበኩላቸው እንደገለጹት ከብዙ ተወዳዳሪዎች መካከል ቪዥን አሉሚነምን የመረጥንበት ምክንያት የሥራውን አስተማማኝነትና የዕቃ ጥራት ቀደም ሲል ለባንካችን በሠራው ሥራ ስላረጋገጥን ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም እንደ አሁን ቀደሙ ሁሉ ሌሎች ሥራዎችን ከቪዥን አሉሚነም ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚህ ቀደም ቪዥን አሉሚነም ኃ/የተ/የግል ማህበር እና ዳሸን ባንክ አክስዮን ማህበር የዳሸን ባንክን ዋና መስሪያ ቤት ባለ 17 ፎቅ ህንጻ የማጠናቀቅ ሥራ ለማካሄድ የ6,295,000.00 የአሜሪካ ዶላር ስምምነት ተዋውለው በውሉ መሠረት ቪዥን አሉሚነም ሥራውን 95% አጠናቆ በተገቢው ጊዜ ለማስረከብ በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡