ዩኒቲ አካዳሚ የማስተማር ሥራ ጀመረ
መስከረም 7 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዩኒቲ አካዳሚ በ2006 ዓ.ም. ከአፀደ ሕፃናት እስከ አራተኛ ክፍል የመጀመሪያ ሳይክል ትምህርት ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቅቆ ሥራ መጀመሩን ይፋ አደረገ፡፡
![]() |
![]() |
![]() |
ወላጆችና ተጋባዥ እንግዶች | ወ/ሮ አሰለፈች ገ/ኪዳን የአካዳሚው ዳይሬክተር | የአካዳሚው የመጫወቻ ስፍራ በከፊል |
የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አካል የሆነው ይኸው ዩኒቲ አካዳሚ ለትምህርቱ መስጫ ባዘጋጀው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ውስጥ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ከወላጆች ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ሲሳይ በተያዘው የትምህርት ዓመት ከአፀደ ሕፃናት እስከ አራተኛ ክፍል የመጀመሪያ ሳይክል ትምህርት ቢጀመርም በየዓመቱ እያደገ እስከ መሰናዶ ትምህርት እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ብርሃኑ አያይዘውም የትምህርት ቤቱ መመሥረት ዋና ዓላማ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሚሰጠው ትምህርት ወጥነት ያለውና በዕውቀት የበለፀጉ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን የጥራት ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ተግባርም አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የዩኒቲ አካዳሚ ዳይሬክተር ወ/ሮ አሠለፈች ገ/ኪዳን አካዳሚው ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን የመመዘኛ መስፈርት መነሻ በማድረግ በበቂ ዝግጅትና በተሟላ ሁኔታ በመደራጀቱ የማስተማር ዕውቅና ያገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ አእምሮአቸው በነጭ ወረቀት የሚመሰለውን ሕፃናት በዕውቀትና በሥነ ምግባር ለማነጽ ኃላፊነት ተረክበናል ብለዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ አካዳሚው ለመማር ማስተማሩ ሂደት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ በመምህራን ቅጥር ላይ በማስተማር ስነ ዘዴ ወይም ፔዳጎጂካል ሳይንስ የሠለጠኑ፤ በማስተማር ልምድ ያካበቱና ደረጃቸው ከፍ ያሉ መምህራን የተቀጠሩ ሲሆን፤ ወደ ሥራ ከመሠማራታቸው በፊት በተማሪ ተኮር የማስተማር ዘዴ፣ በትምህርት ዕቅድ አዘጋጃጀት፣ በፈተና ምዘናና ግምገማ ስልቶች እንዲሁም በክፍል አያያዝና አደረጃጀት ላይ ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ወርቅአለማሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ በየደረጃው ትምህርት ለመስጠት በቁርጠኛነት መነሳቱ ወጣቶች በተሻለ ሥነ ምግባርና ዕውቀት ታንጸው ለሀገር ገንቢ እንደሚሆኑ ራዕይ ሰንቆ መነሳቱን ያመለክታል ብለዋል፡፡
አቶ ደረጃ አያይዘውም አካዳሚው በመማር ማስተማሩ መስክ ለሚያደርገው የተሳካ እንቅስቃሴ አስተዳደሩ ማናቸውንም ድጋፎች እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ወላጆች፣ መምህራኖች፣ የትምህርት ቤቱ አስዳደር ሠራተኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፣ በተለይ ወላጆች አዲስ የተጀመረው አካዳሚ ልጆቻቸውን በዕውቀትና በሥነ ምግባር አንጾና ደህንነታቸውን ጠብቆ ለጥሩ ደረጃ እንደሚያደርስላቸው እነርሱም አጋዥ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡