ኅብረትና የቡድን
ሥራ ለውጤት የሚያበቁ
ናቸው፡፡ እያንዳንዷ
የሠንሰለት ተቀጣይ
አካል የጠቅላላው
ሠንሰለት ጥንካሬ
መለኪያ የመሆኗን
ያህል፣ የአንድ
ተጫዋች ብቃት፣
ችሎታና ጥንካሬ
ወይም ድክመት ለአንድ
የስፖርት ቡድን
ጥንካሬ ወሳኝነት
አለው፡፡ ስኬታማነት
በውጤት በሚለካበት
ዓለም ውስጥ ውጤት-ተኮር
የሆነን ድርጅት
ምርታማ አድርጎ
ለመምራት ስፖርትን
ለማኔጅመንት መሣሪያና
ምሳሌ አድርጎ መጠቀም
አስፈላጊ ነው፡፡
በዚህ ዕምነት መነሻነትና
የሠራተኞቻችንን
ሞራል ለማዳበርና
ቡድናዊ የቅንጅት
ሥራን ለማጠናከር
ባለን ዓላማ ከሦስት
ዓመታት በፊት በሁሉም
ኩባንያዎቻችን ውስጥ
የስፖርት ቡድኖች
እንዲመሠረቱ አድርገናል፡፡
በዚህ ዓመት ደግሞ
ተጨማሪ እርምጃ
በመውሰድ ስፖርታዊ
እንቅስቃሴዎችን
የሚያስተባብሩ የሥራ
ኃላፊዎችን በመመደብና
ከሁሉም ኩባንያዎቻችን
የተውጣጡ ሠራተኞችን
ብቻ በተጫዋችነት
በማሰባሰብ የ“መቻሬ”
ስፖርት ክለብን
መሥርተናል፡፡ የ“መቻሬ”
እግር ኳስ ቡድን
በአዲስ አበባ እግር
ኳስ ፌደሬሽን ከተመዘገቡት
የከፍተኛ ዲቪዚዮን
ክለቦች አንዱ በመሆን
የመጀመሪያ የውድድር
ግጥሚያውንም ጥር
22 ቀን 1996 ዓ.ም. በማካሄድ
ተግባሩን ጀምሯል፡፡
እንደተጠበቀውም
ቡድናችን ሠራተኞቻችንን
አስተባብሮ የሚያገናኝ
አካል በመሆን ላይ
ይገኛል፡፡ የአንድ
ቡድን አመራር ልክ
አንድ ድርጅትን
የመምራት ያህል
ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው
መሆኑን ለማመላከት
እንዲቻል ዝርዝር
የሥራ አፈጻጸም
መመሪያ ለሁሉም
የኩባንያዎቻችን
ሠራተኞች እንዲተላለፍ
ተደርጓል፡፡ ስፖርት
በተለይም በሠራተኞቻችን
ለሠራተኞችና ለድርጅት
አርአያ ለመሆንና
ኅብረትን ለማጠናከር
የተቋቋመና የተሰለፈ
ቡድናችን፤ በማሸነፍና
በመሸነፍ ብቻ ተግባሩ
የሚለካ መሆን እንደሌለበት
ባስገነዘብኩበት
ደብዳቤዬ ውስጥ
እንደተዘረዘረው፤
ቡድናችን ከሌሎች
የሚለይበት የራሱ
የሆነ ልዩ የተግባር
መለያ በመፍጠር
በተመልካቹ ዘንድ
በናፍቆትና በፍቅር
የሚጠበቅና የሚታይ
እንዲሆን ልዩ አሠራርና
አካሄድ ያስፈልገዋል፡፡
በዚህም መሠረት
የሚከተሉት ዐበይት
ጉዳዮች ለቡድናችን
የመለያ ተግባሮች
እንዲሆኑ በደብዳቤው
ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን
ነጥቦች ቡድናችን
በተግባር እንዲያውላቸው
የመላ ሠራተኛው
ድጋፍና ተከታታይነት
ያስፈልጋል፡፡
እነዚህ የትኩረት
ነጥቦቻችን በየኩባንያዎቻችንም
ውስጥ በምናካሂዳቸው
ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች
ተግባራዊ ሊሆኑ
ይገባል፡፡ በመሆኑም
አበረታች በሆነው
ጅማሬያችን ይበልጥ
ተጠናክረን በመግፋት
ካለምንበት ግብ
በተሳካ ሁኔታ እንደምንደርስ
ያለኝ ዕምነት ከፍተኛ
ነው፡፡ ሠራተኞች
በስፖርት የሚሳተፉት
ለስፖርት ፍቅር
ባላቸው ግፊት መሆን
አለበት፡፡ ስፖርተኝነት
ከቋሚ የኩባንያ
ምድብ ሥራ በተጨማሪ
የሚከናወን የግለሰቡ
ተግባር ሲሆን፣
ኩባንያዎቻችን ሠራተኛውን
ይህን ተጨማሪ ተግባር
(Extra curricular activity) እንደአስፈላጊነቱ
ይደግፋሉ፡፡