የሕዝብ ፍቅርንና ተወዳጅነትን አትርፈዋል፤ መልካም ምግባራቸው፣ ልግስናቸውና ሀገርን ለማሳደግ የሚያደርጉት የዘወትር ጥረት በብዙዎች ልብ ውስጥ የከበረን ሥፍራ እንዲይዙ አስችሏቸዋል፡፡ በተለያዩ በጎ ተግባራቸው በሀገራችን የታሪክ መዝገብ ስማቸው በክብር ሰፍሯል፡፡ እኚህ ታላቅ ሰውና ስመ-ጥሩው ሊቀመንበራችን ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በስማቸው የተሰየመውን ሴካፋ አል-አሙዲ ሲንየር ቻሌንጅ ካፕ ለ3 ዓመታት ስፖንሰር በማድረግና «28ኛው የሴካፋ አል-አሙዲ ሲንየር ቻሌንጅ ካፕ» በአዲስ አበባ ውስጥ እንዲካሄድ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ የተዳከመውን የክፍለ-አህጉሩን የእግር ኳስ ስፖርት ለዳግም ውልደት አብቅተውታል፡፡
ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን የምዕተ-ዓመቱ የክብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሼክ ሙሐመድ ውድድሩ በተጀመረበት ዕለት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንክሮ በመጫወት ዋንጫውን በሀገሩ እንዲያስቀር ተመኝተዋል፡፡ ይህ ምኞት ዕውን ሆኖ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ በመሆን ዋንጫውን አስቀርቷል፡፡ ውጤቱን በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው ሕዝብ በሼክ ሙሐመድ ስም በተሰየመው ውድድር አሸናፊ ለመሆን በመብቃቱ የተሰማውን ድርብ ደስታ ገልጿል፡፡ የሴካፋ ውድድርን ስፖንሰር ያደረጉት ሊቀመንበራችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድናችን ውድድሩን በድል በማጠናቀቁ በተለመደው ችሮታቸው ለእያንዳንዱ ተጫዋች 50 ሺህ ብር ሽልማት ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም ለብሔራዊ ቡድናችን 35 ሺህ ዶላር፣ ሁለተኛ ለወጣው የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን 20 ሺህ ዶላር፣ ሦስተኛ ለወጣው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን 10 ሺህ ዶላር፣ አራተኛ ለወጣው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን 5 ሺህ ዶላር አበርክተዋል፡፡ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሲኢኦ ቢሮም ከሊቀመንበሩ በተሰጠው መመሪያ መሠረት ለእያንዳንዱ ቡድን ማመላለሻ መኪና ከአሽከርካሪ ጋር በመመደብ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
የአዲስ አበባ መስተዳድር ቦታ ከሰጠ አዲስ ስታድየም መሥራትን በሚመለከት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የበኩላቸውን ግዴታ እንደሚወጡ ሊቀመንበራችን ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር ቦታውን ለመስጠት ወዲያውኑ ስምምነቱን የገለጸ ሲሆን፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ የተገኘውን ድል ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተገኙበት በሸራተን አዲስ በተደረገው የእራት ግብዣ ላይ በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ከንቲባ አርከበ ዕቁባይ ለስታዲየም መሥሪያ ቦታ ካርታን ለወጣቶች፣ ስፖርትና ባህል ሚኒስትር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ አስረክበዋል፡፡
በ28ኛው የሴካፋ አል-አሙዲ ሲንየር ቻሌንጅ ካፕ ፍጻሜ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ለአሸናፊው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተዘጋጀውን ዋንጫ የሰጡት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከንቲባ አርከበ ዕቁባይ፣ የአቅም ግንባታ ሚኒስትር አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ የወጣቶች ስፖርትና ባህል ሚኒስትር አቶ ተሾመ ቶጋ፣ ሊቀመንበራችን ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አል-አሙዲ፣ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሲኢኦ ዶ/ር አረጋ ይርዳው፣ የሴካፋ ፕሬዚዳንትና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ውድድሩ በይፋ በተዘጋበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሲኢኦ ቢሮ በሥሩ ያሉ ኩባንያዎችን በማስተባበር የዋንጫ ጨዋታውን ጨምሮ ሌሎች ውድድሮች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተላልፈው ለሕዝብ ዕይታ እንዲበቁ ስፖንሰር በማድረግ ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ሽልማት የተበረከተለት ሲሆን፤ ይህንንም ሽልማት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ተቀብለዋል፡፡