በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በአዳማ ..ናዝሬት.. ከተማ ሊቀመንበራችን ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ በለገሱት ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ የተገነባው የኦሮሞ ሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት መጋቢት 16 ቀን 2000 ዓ.ም. በተከናወነው ታላቅ ሥነ-ሥርዓት ተመርቋል፡፡
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ክቡር ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል መስተዳድሮች ባለሥልጣናት የተገኙ ሲሆን ክቡር ሼህ ሙሐመድን በመወከል የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው፣ አቶ አብነት ገብረ መስቀልና ሌሎችም የሚድሮክ ኢትዮጵያ የሥራ ኃላፊዎች የበዓሉ ተካፋይ ሆነዋል፡፡ በናዝሬት ከተማ መግቢያ ላይ ባለው ከፍታ ሥፍራ በ64 ሔክታር ክልል ላይ የተገነባው ይህ ሐውልት በዙሪያው ቋሚ የኤግዚቢሽን ማዕከል፣ የትያትር አዳራሽና የተለያዩ ቢሮዎች፣ የምርምር ማዕከልና ቤተ መጻሕፍት እንዲሁም የመዝናኛ ሥፍራዎችና የእንግዶች ማረፊያ የሚገኙበት ሲሆን ከ63.9 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ነው፡፡ የሚድሮክ ኢትዮጵያ እህት ኩባንያ በሆነው በሚድሮክ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር ተገንብቶ በዕለቱ የተመረቀው ይህ ሐውልት እውን ሊሆን የቻለው ሊቀመንበራችን በለገሱት 50 ሚሊዮን ብር እንደሆነ በመጥቀስ የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ታላቅ ምሥጋናን አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ " ለምወዳት ሀገሬና ለሕዝቦችዋ የተሻለ ሕይወት የበኩላቸውን ድርሻ ሲወጡ ሕይወታቸውን ላጡ ሰማዕታት የመታሰቢያ ሐውልት ሲቆምላቸው የትግሉ አካል ለመሆን በገንዘቤ የበኩሌን አስተዋፅኦ አበረክታለሁ" በማለት ልግስና ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህም የኦሮሞ ሕዝቦች ትግል አጋርና ጀግና ለመሆን አብቅቷቸዋል በማለት በመላው የኦሮሞ ሕብረተሰብ ስም ፕሬዚዳንቱ የአክብሮት ምሥጋናቸውን ለሊቀመንበራችን አስተላልፈዋል፡፡በዚህ ሥነ-ሥርዓት ማብቂያ ላይ በሐውልቱ ሥራ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱት ልዩ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ለሊቀመንበራችን ለሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲን ከፍተኛ ደረጃ የሚሰጠው ከወርቅ የተሠራ ልዩ ሜዳሊያ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሜዳሊያውንም ዶ/ር አረጋ ይርዳው ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ከአቶ አባዱላ ገመዳ እጅ ተቀብለዋል፡፡
ይህ ሽልማት ለሊቀመንበራችን አስተዋፅኦ ተገቢውን ክብር የሚሰጥ ሲሆን፣ ሼህ ሙሐመድ እያደረጉ ባሉት ተሳትፎ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለያዩ ዞኖች በልማት እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ለምንገኘው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኩባንያዎች ማኔጅመንትና ሠራተኞች የተለየ ክብርና ኩራት ይሰማናል፡፡