BACK TO HOME PAGE BACK TO NEWS HIGHLIGHTS
     
ከሠራተኞች ለሊቀ መንበራችን የተዘጋጀውን ስጦታ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ለሼክ ሰዒድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ሲያስረክቡ
 
ሼህ ሰዒድ የመታሰቢያውን ችግኝ ሲተክሉ
 
አቶ ቡሰሪ የመታሰቢያውን ችግኝ ሲተክሉ
 
ዶ/ር አረጋ ይርዳው የመታሰቢያውን ችግኝ ሲተክሉ
 
   
የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የልደት ቀን በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሠራተኞች ተከበረ
July 21, 2008
 
 
 
በሀገራችን የግል ኢንቨስትመንት ታሪክ ውስጥ ስማቸው በጉልህ የሚጠራውና ስኬታማነታቸው የማያጠራጥረው ብርቅዬ የሀገር ልጅ የሆኑት የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤትና ሊቀመንበር የልደት ቀን ሐምሌ 14 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ሠራተኞች በደማቅ ሁኔታ ተከብሮአል፡፡የዘንድሮው “የሊቀመንበር ቀን” በሚሊኒየማችን ዓመት መከበሩን ምክንያት በማድረግ ልዩ ግምት በመስጠት በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት የተከበረ ሲሆን ዕለቱም ለታሪክ እንዲበቃ የማስታወሻ ዛፍ ችግኞች ተከላ በሊቀመንበራችን፣ በቺፍ ኤግዚክዩቲቭ ኦፊሰራችንና በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ 15 ኩባንያዎች ስም ተካሂዷል፡፡ቀደም ሲል በዚህ ፕሮግራም ላይ የማኔጅመንቱና የሠራተኞች ተወካዮች ንግግር ያደረጉ ሲሆን ማኔጅመንቱን በመወከል አቶ ጌታቸው ሐጎስ የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባደረጉት ንግግር “ሊቀመንበራችንን በአንድ ድምፅ እንኳን ለልደት በዓላቸው አደረሳቸው በማለት፤ ወደር የሌለው ደስታችንን ስንገልፅ ልዩ ደስታ እየተሰማን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ እንዳስረዱት የሊቀመንበርን ቀን በየዓመቱ በቋሚ በዓልነት ስናከብር ለእኛ ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች የማኔጅመንት አባላት ልዩ ትርጉም የሚፈጥርልን ዕለት ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ዕለት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢንቨስትመንት ስኬታቸውን የምናበስርበት፣ ለሀገር ልማት ያበረከቱት ሰፊ አስተዋጽኦ የሚወደስበት፣ የወገን አለኝታነታቸውን እውነተኛ ምሥክርነት የምንዘክርበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በዘመናዊ ማኔጅመንት ሥርዓት ውስጥ እንድንመራ አብሮ አደጋቸውንና ልዩ የመሪነት ችሎታ ያላቸውን ዶ/ር አረጋ ይርዳውን በቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰርነት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ መስጠታቸውን የምናመሰግንበት፣ እንዲሁም በየዓመቱ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ሠራተኞች ከቤተሰቦቻችን ጋር በመሆን ይህንን በዓል ስናስብ ለሊቀመንበራችን ረጅም እድሜ እንዲሰጥልን በየእምነታችን የምንማፀንበት ዕለት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በማለት አብራርተዋል፡፡

“የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበርና ባለቤት የሆኑት ሼክ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በዓለም እና በልዩ ሁኔታም በኢትዮጵያ እያካሂዱ ያሉት ኢንቨስትመንት በቀጥታ ተጠቃሚ የሆነውን የኩባንያዎቹን ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ለሀገር እድገት የሚቆረቆር ዜጋን ልብ በኩራት ይሞላል፡፡ በግሉ የኢንቬስትመንት ዘርፍ በሀገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሠራተኛ አቅፎ የሚገኘው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቬስትመንት ሲሆን የሊቀመንበራችን የልደት ቀን ዓመታዊ በዓል በመሆን ማክበር ከጀመርን አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም ዕለት መላው ሠራተኛና ቤተሰቡ እንኳን ለልደት በዓላቸው በሰላም አደረሳቸው የሚለውን የሠራተኞች መልዕክት ዶ/ር አረጋ ይርዳው እንዲያደርሱልን ስጠይቅ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡” ብለዋል፡፡ በዕለቱ በተካሄደው ፕሮግራም በሲ.ኢ.ኦ ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች የሆኑት አቶ ለገሰ ተ/ማርያም የፋይናንስና ማቴሪያልስ ማኔጅመንት አገልግሎት ኃላፊና ወ/ት ዕፀሕይወት ድንቁ የማርኬቲንግ ሴልስና ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት አገልግሎት ኃላፊ በየበኩላቸው ባደረጉዋቸው ንግግሮች የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴና ያሳዩዋቸውን እድገቶች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ በዚህ ገለፃ መሠረት ከስምንት ዓመታት በፊት አምስት የነበረው የኩባንያዎቹ ቁጥር በአሁኑ ወቅት 15 የደረሰ ሲሆን፤ የሠራተኛ ብዛት ከ5500 በላይ በመድረስ የ30 ከመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ዓመታዊ የደመወዝ ክፍያው ከብር 33.6 ሚሊዮን ወደ 64.3 ሚሊዮን ያደገ ሲሆን የ90 ከመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ሽያጩም ከ491.8 ሚሊዮን ወደ ብር 1.36 ቢሊዮን በማደግ በ175 ከመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ቀደም ሲል የመነሻው ኢንቬስትመንት ብር 3.77 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን፤ በዚህ የስምንት ዓመታት ጊዜ በተጨማሪ ብር 1.09 ቢሊዮን ኢንቬስት ተደርጓል፡፡ ይህም አጠቃላዩን ኢንቬስትመንት ወደ ብር 4.86 ቢሊዮን ያደርሰዋል፡፡

 
All Contents © Copyright MIDROC Ethiopia, Office of the Chief Executive Officer, 2008. All Rights Reserved.