BACK TO HOME PAGE BACK TO NEWS HIGHLIGHTS
 
 
 
   
የሠራተኛ ማኅበራት የዘመናዊ ማኔጅመንት አጋዥ ኃይል ናቸው
EXTRACTED FROM MIDROC NEWSLETTER ISSUE NO. 48
January—February, 2009
DR. AREGA YIRDAW, CHIEF EXECUTIVE OFFICER, MIDROC ETHIOPIA  
 
     

ከስምንት ዓመታት በፊት የጀመርነው ዘመናዊ የማኔጅመንት ሥርዓት ቀስ በቀስ አድጎ በአሁኑ ወቅት 16 ኩባንያዎቻችንን አስተባብሮ ለመምራት የተቻለበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በሚል መለያ የሚታወቁት እነዚህ ኩባንያዎቻችን በተለያዩ አቅጣጫዎች በአርአያነት ሊወሰዱ የሚችሉ አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮችን በሀገራችን ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ መስክ በሥራው ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በሆኑት ሁሉ ታላላቅ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ኩባንያዎቹ የቆሙላቸውን መሠረታዊ ዓላማዎች ከግባቸው ለማድረስ የሚያበቁዋቸውን ልዩ ልዩ ፖሊሲዎች ነድፈን ..ሰው ተኮር.. የሆነ የማኔጅመንት ሥርዓት ተግባራዊ ስናደርግ በማኔጅመንቱና በሠራተኛው መካከል ሊኖር የሚገባውን ጤናማ ግንኙነት በፅኑዕ መሠረት ላይ በመጣል ነው፡፡የሠራተኛ ማኅበራት ለኩባንያዎቻችን ሊሰጡ የሚችሉትን ድጋፍ በሚገባ ስለምናውቅ የኩባንያዎቻችን ሠራተኞች የሠራተኛ ማኅበር እንዲያቋቋሙና እንዲደራጁ ማኔጅመንቱ ድጋፍ መስጠት ብቻ ሳይሆን ግፊት አድርጓል፡፡ማኅበራትን ያቋቋሙ ኩባንያዎችም እንዲጠናከሩ በማድረግ ኩባንያዎቻችን እድገት እንዲያስመዘግቡ የሚረዳ ኢንዱስትሪያዊ ሰላም አስፍነናል፡፡ በዚህ ጥረት ከኩባንያዎቻችን መሀከል መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበራት ያላቸው ስምንት የደረሱ ሲሆን የእነዚህ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች የመመካከሪያ መድረክ በማቋቋም ማኅበራት ልምድ የሚለዋወጡበትና አቅማቸውን የሚያጠናክሩበት መድረክ መፍጠራችን ታላቅ ክንዋኔ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ማንኛውም ኩባንያ ተልዕኮውን ለመወጣትና ትርፋማነቱን ለማረጋገጥ በቅድሚያ የሥራ ታታሪነትና ፍላጎት ያላቸው ሠራተኞች ሲኖሩት በመሆኑ የማኔጅመንቱና የሠራተኛው ማኅበር እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ በጀመሩት የእድገት ጎዳና እንዲራመዱ ማስቻል ስኬታማ ጥረታችን ሆኗል፡፡ያለ ሠራተኛ የኩባንያ ዕድገት ከቶውንም የሚታሰብ ባለመሆኑ ሠራተኛው በጥንካሬ እንዲንቀሳቀስና ወደ ትርፋማነት ደረጃ እንዲሸጋገር በማነጅመንትና በሠራተኞች መካከል እየዳበረ የሚሄድ ዘመናዊ አስተሳሰብንና ጥበብን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ሠራተኛውና የሥራ ኃላፊዎች በጋራ ሊጠቀሙበት የሚችሉት የሕብረት ስምምነት የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች የማኔጅመንቱን ዘመናዊ የሥራ ፖሊሲዎች በማጥናትና ተግባራዊ በማድረግ በድርድር መልክ የተቀረፁትን የህብረት ስምምነት መሠረታዊ ሀሳቦች በማስክበር ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡የሠራተኛ ማኅበራት በጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀር የደብዳቤ ልውውጥ ከማድረግና ስብሰባዎችን ከማብዛት አጉል ባህል ተላቅቀው የድርጅቶቻቸውንና የሠራተኞችን ሕልውና በሚያስጠብቁ ተግባራት ላይ በማተኮር ምርታማነት እንዲዳብር በቁርጠኝነት የተሰለፉ መሆን ይገባቸዋል፡፡ የሠራተኛ ማህበራት ማኔጅመንቱን ተክተው የሚሠሩ ሳይሆኑ በኩባንያዎች የሰው ኃይል አገልግሎት ፖሊሲዎችና በህብረት ስምምነት አንቀጾች ላይ በመመርኮዝ ሰው ተኮር ለሆነውና የሠራተኛውን ጥቅም ለሚያከብረው ማኔጅመንት አጋዥነታቸውን የሚያረጋግጡ አካሎች መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡በአሁኑ ወቅት በታሪካዊ አስፈላጊነታቸው ሕልውናቸው የሚታወቀው የሠራተኞች ፌዴሬሽንም ሆኑ የአሠሪዎች ፌዴሬሽን አካላት ዋነኛ ዓላማቸው ምርታማነት የሚያድግበትን ሁኔታ በማመቻቸት ላይ ብቻ ማተኮር ይኖርባቸዋል፡፡በኩባንያዎች ሕይወት ውስጥ ሠራተኞችና አሠሪዎች የሚለው ክፍፍል በዘመናዊ የማኔጅመንት ሥርዓት እየቀረ እንደሚሄድና ሁሉም ሠራተኞች ሆነው ራሳቸውን በመቻል ከየትኛውም የውጭ ..አስታራቂ ኃይል ርዳታ ሳያስፈልጋቸው የሚኖሩበት የምርታማነት ሥራ ዓለም ውስጥ እንደምንገባ አምናለሁ፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የቴክኖሎጂ ግሩፕ ሠራተኞች የተገበሩት ይህንኑ ነው፡፡ ወደፊትም ይህንኑ እያጠናከርን ሰዎች በሥራ ምድባቸውና በሚያደርጉት አስተዋጽኦ መጠን ተከብረውና የድርጅቱ አካል ሆነው በደስታ እንዲሠሩ ሂደቱ እየተጠናከረ ይሄዳል፡፡

  CEO'S MESSAGES ARCHIVES
 

* For additional archives you may contact us (click here)

 
All Contents © Copyright MIDROC Ethiopia, Office of the Chief Executive Officer, 2008. All Rights Reserved.