BACK TO HOME PAGE BACK TO NEWS HIGHLIGHTS
     
   
     
   
ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ወደ ሚድሮክ ኢትዮጵያ በመተላለፍ የቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎችን ተቀላቀለ  
NOVEMBER 25, 2008
 
 
 

በሀገራችን ታላላቅ የኤኮኖሚ ዘርፎች ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግና በተለያዩ የግንባታ መስኮች ጉልህ ድርሻን በማበርከት ላይ የሚገኙት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበር ሼኽ መሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ አንድ ተጨማሪ እርምጃ በመውሰድ በሀገራችን የመጀመሪያውና ታላቅ የግል ዩኒቨርስቲ የሆነውን ዩኒቲ ዩኒቨርስቲን የባለቤቶቹን የአክሲዮን ድርሻ በመግዛት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች 16ኛው ኩባንያ እንዲሆን አደረጉ፡፡

ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት ብቸኛው የሀገራችን የግል ዩኒቨርሲቲ በመሆን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ረፐብሊክ የትምህርት ሚኒስቴር ሙሉ ዕውቅና የተሰጠው የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቅዋም ሲሆን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ምሁራንን በማፍራት በግሉ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ የዕድገት ጎዳና ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ተቅዋም ነው፡፡ የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ ባለቤቶችና "የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር" አክስዮን ባለሀብቶች ኅዳር 12 ቀን 2001 ዓ/ም ጉዳዩ በሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ዘንድ ቀርበው በተደረገው ስምምነት መሠረት አክስዮኖቻቸውን በጠቅላላ በመሸጥ የዩኒቨርስቲው ባለንብረትነት ወደ አዲሶቹ ባለአክስዮኖች እንዲዛወር አድርገዋል፡፡

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበርና የኩባንያዎቻችን ባለሀብት የሆኑት ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የሚወዷት ሀገራቸውንና ሕዝቦችዋን ለተሻለ ሕይወት ባለቤትነት ለማብቃት በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ-ንዋያቸውን ሲያፈሱ የተወሰነና ምናልባትም ትርፋማ ነው ተብሎ በሚታመንበት የንግድ ሥራ ዘርፍ ላይ ብቻ በማተኮር አይደለም፡፡ ለሕብረተሰቡ ይበጃል የተባለውን ሁሉ ለማድረግና የተጠየቁትን ለመፈፀም ያመነቱበት ጊዜ የለም፡፡ በመሆኑም በተለያዩ አጋጣሚዎች ለበረካታ ግለሰቦች፣ መንግሥታዊና ማህበራዊ ተቅዋሞች በሚሊዮኖች የሚቆጠር በልግስና የሰጡ ሲሆን በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን ልማት፣ በኮንስትራክሽን፣ በየብስና አየር አገልግሎት፣በጤናና በትምህርት ወዘተ.የተሰማሩ ኩባንያዎቻቸውን ለሀገር ልማት ፈጥረዋል፡፡ በትምህርት ዘርፍ እስከዛሬ ድረስ በተደረጉት ጥረቶችና በሊቀመንበራችን ልዩ ችሮታ በሀገር ውስጥና ከሀገር ወጭ ተልከው ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉ በርካታ ወገኖቻችን መኖራቸው ሳይዘነጋ ..ሰላም የነርሶች ኮሌጅ..ን አጠቃላይ ገፅታና በጤናው ዘርፍ ባለሙያዎችን ለማፍራትና ወገኖቻችንን ለመርዳት ነፃ የትምህርት ዕድል ለብዙ ዜጎች በመስጠት ያበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡

በዛሬው ዕለት የዩኒቲ ዩኒቨርስቲን የባለቤትነት ዝውውር በምናበስርበት ወቅት ሚድሮክ ኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ ላለው ራዕይና ተልዕኮ ተገቢውን አፅንኦትበመስጠት ነው፡፡ በማንም የማይበለጥ ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ለተጠቃሚው የማቅረብ ትልማችንን በትምህርቱም ዘርፍ ተግባራዊ ለማድረግ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲን የመሳሰሉት ተቅዋሞች ያስፈልጉናል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቅዋም ባለቤቶች መሆናችን ለዚህች ሀገር የትምህርት ጥራትና ዕድገት የምናልመውን ዕውን ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርልናል ብለን እናምናለን፡፡ የትምህርት ጥራት እንዲኖርና እንዲዳብር ለማድረግ በተግባር ሊፈተንና በማሕብረሰባዊ ጠቃሚነቱ ሊረጋገጥ የሚችል ሥርዓተ-ትምህርት፣ ብቃትና ጥራት ያላቸው መምህራንና ለመማር ማስተማር የሚያስፈልጉት ግብአቶች ተሟልተው መገኘታቸው ወሳኝነት አላቸው፡፡ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲን በባለቤትነት ስንረከብ እነዚህ ኃላፊነቶች እንዳሉብን በማወቅና ለሀገራችን የትምህርት ጥራትና አቅም ግንባታ ባለን ቁርጠኛ ፍላጎት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንድንችል ለማድረግ ነው፡፡

ለአንድ ሀገር እድገት የትምህርት ጠቀሜታ ሊረጋገጥ የሚችለው የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች መሪ ሊሆኑ የሚችሉና ለኢንዱስትሪያዊ እድገት ቁልፍ ድርሻ የሚኖራቸውን ምሁራን ማፍራት ሲቻል ነው፡፡ የትምህርት ተቅዋማት በንድፈ-ሀሳባዊ ዕውቀት የደረጁ ሲሆኑ በማምረት ተግባር ላይ ያሉት እንዲስትሪያዊ ተቅዋማት በልምድ የበለፀጉ የዕውቀት ጎተራዎች ናቸው፡፡ የሁለቱ ጥምረት የሚፈጥረው ድምር ሀብት የትምህርቱን ዘርፍ የማይጠወልግ ዕውቀት ምንጭ ባለቤት ስለሚያደርገው የሀገር እድገት የማያወላውል መሠረት ይኖረዋል፡፡ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲያችን የንድፈ-ሀሳብንና ተግባርን ጥምረት፣የአካዳሚውንና የአምራች እንዱስትሪውን የተቀናበረ የእድገት ትልም የሚያስገኝ ተቅዋም ስለሚሆን ለሀገራችን ተጨማሪ ልምድ ለማካበት የሚረዳ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በየፋብሪካዎቻችን ያሉት ምሁራን በተግባር የተፈተነ ዕውቀታቸውን ለአዲሱ ትውልድ በተጨባጭ የሚያስተምሩበትና በክፍል ተወስነው በቀለም ዕውቀት ብዙ የተራመዱት ደግሞ የተጨባጩን ዓለም ግዙፍ ልምድ በተግባራዊ ተሳትፎ የሚያጠኑበት ልዩ ዓለም ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ያስገኝልናል ብለን እናምናለን፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቅዋሙ መምህራን በእንዱስትሪያዊ የፋብሪካዎች የምርት ሒደት ተግባራዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ለዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ከእንግዲህ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ፋብሪካዎች ለእድገታቸው የሚያስፍልጓቸውን ምሁራን ከመነሻው ለማዘጋጀት ዕድሉ ሲፈጠርላቸውና ተማሪዎችም ወደ ሥራ ዓለም ሲሸጋገሩ የሚያደናግራቸው አካባቢ እንዳይኖር የበቂ ልምድ ባለቤቶች ሲሆኑ የምናይበትም አጋጣሚ ይፈጠራል ፡፡

በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው የግል ዩኒቨርስቲ በመሆንና በሥራ ዓለም ምስጉን የሆኑ ምሁራንን በማፍራት ላይ ያለው ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎችን የመቀላቀሉ ብሥራት ለሁሉም የሀገራችን ሕዝቦች ትምህርትን ለማዳረስ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ዐቅም ሊኖረው የሚችል አንድ አጋር መፈጠሩንም የሚያመለክት ይሆናል፡፡ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ትምህርት የጠማውን የሕብረተሰባችን ክፍል ለማርካት በሚደረገው ጥረት ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን በርካታ ቅርንጫፎችን በመፍጠርና በጥራት ላይ የተመረኮዘ የርቀት ትምህርት ፕሮግራሙን በአዲስ መልክ አደራጅቶ የእስከዛሬውን በማጠናከር ዘርፈ ብዙ አገልግሎት አበርክቷል ያበረክታልም፡፡ ሚድሮክ ኢትዮጵያም ሠራተኞችን ለቀጣይ ትምህርት በመላክ በዩኒቨርስቲው መጠቀም ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ይህ ተግባር ወደፊትም በስፊው ይቀጥላል፡፡

በመጨረሻም በተለያዩ ዘርፎች ሀገራዊ የልማት አጋርነቱን በተግባር እያረጋገጠ የሚገኘው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በትምህርት ዘርፍ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዕድሉን ለሰጡት ዕውቁ የሀገራችን ታላቅ ኢንቨስተር ለሼኽ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲና ቤተሰቦቻቸው ምስጋናችንን እያቀረብን የኚህን ብርቅዬና እውነተኛ የሀገራችን ልጅ ምኞት ለማሳካት በቁርጠኝነት የምንሠራ መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡ መላውን የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብም እንኳን ወደ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ማሕበረሰብ ደህና መጣችሁ እንላለን፡፡

የመጀመሪያው የግል ዩኒቨርስቲን ያስገኘው የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር 16ኛው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያ መሆኑንም በታላቅ ደስ እያበሰርን በሥራ፣ በትምህርትና በቅንነት የልማት አጋርነታችንን አጠናክረን እንደምንቀጥል እናረጋግጣለን፡፡

 
All Contents © Copyright MIDROC Ethiopia, Office of the Chief Executive Officer, 2008. All Rights Reserved.